Service Times: Sundays 10 am - 1 pm

Ministries

WHERE TO SERVE

Our Ministries

የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ክፍሎች

የቃሉ አገልግሎት

‹‹ቃሉን ግልጽ፣ ትክክልና የጠራ አድርጎ በማቅረብ ለሕይወት ለዋጭ ግብ መሥራት›› ነው። ይህንንም የሚያደርገው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን) በትምህርትና በስብከት እንዲዳሰስ ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ ነው። ይህንንም ተዛማጅ የሆኑ ተግባራዊና ታሪካዊ እውነቶች ለምእመኑ እንዲቀርቡ በማድረግ ይፈጽማል።ቃሉ ክህነታዊና ነቢያዊ ሚዛንን በጠበቀ ሁኔታ አማኞችን እንዲያገኛቸው ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ቤተክርስቲያን የምትጠራና የምታንጽ እንድትሆን በቃሉ ውስጥ የድነት መልእክት እንዲጠቃለልና የወንጌል ጥሪ ሆን ተብሎ እንዲደረግም ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል። መጽሐፍ ቅዱስ በሥላሴያዊ እይታ እንዲነበብና ቤተ ክርስቲያንም የሥላሴ ማኅበርተኛ መሆኗን ለሚያሳውቅና ለሚያለማምድ መንፈሳዊ እሴት እየሠራ ተልእኮውን ይወጣል። ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ጊዚያቸውን ጠብቀው ለምእመኑ መቅረባቸውን እየተከታተለና ድግግሞሽ እንዳይኖር ተገቢውን ጥንቃቄ እየወሰደ ምእመናን ሚዛናዊ እንክብካቤ እንዲያገኙ ያደርጋል፣

የዝማሬ አገልግሎት

መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ደጋግሞ የሚያስተዋወቅን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚዘምር ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ ዝማሬም አምላክና ሰው ያስተሳሰረ ድንቅ የመለኮት ሥራ መሆኑን በተደጋጋሚ ያበሥራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬ ትኩረቱን እግዚአብሔር ላይ ያደረገ፣ ከእርሱ የሚመነጭ፣ የእርሱን ረቂቅ ሥራ ገላጭና እርሱ በመረጠው ሁኔታ ፍጡርንና ፈጣሪን የሚያሳትፍ የአምላክ ሥራ ነው፡፡ በመሆኑም የቤተክርስቲያናችን የዝማሬ አገልግሎት በማራኪ ሙዚቃዊ ቅንብር የተደራጀ፣ ለባሕላዊ እሴቶቻችን እውቅና የሰጠ እንዲሁም ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ አምልኮን የሕይወት ዘይቤ ያደረገ ዝማሬ አገልግሎት ለመስጠት ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

ዲቁና አገልግሎት

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዲያቆናት አገልግሎት ብቅ ያለው በጊዜው የተከስተ ችግር ለመፍታት ጥረት በተደረገ ጊዜ ነበር (የሐዋ 6፡1-6)፡፡ ከዚያም በኋላ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን ተልእኮ ለመወጣት የዲያቆናት የአገልግሎት ድርሻ ወሳኝ ሚና እንዳለው ሲታሰብ አግሎግሎቱ በዚያን ወቅት አዲስ በተተከሉ ቤተ ክርስቲያናትም ቀጠለ፡፡ ታሪካቸው ሲጀምር ከሐዋርያት ጋር ተደጋጋፊ ሆኖ ማገልገል ነበር፡፡ በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን ሂደት ዲያቆናት ተጠሪነታቸው ለሐዋርያት ሆኖ መንፈሳዊውን አገልግሎት በማቀላጠፍ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ የሐዋርያት አገልግሎት በሂደት በሽማግሌ፣ በእረኛ ወይም በኤፒስ ቆጶስ በተተካ ጊዜ ዲያቆናት ከሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት አገልግሎታቸውን እንደተወጡ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስተምረናል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምናየቸው ቢሮዎች የሽማግሌዎችና የዲያቆናት ቢሮዎች ናቸው (ፊሊጵ 1፡1) ፡፡ ይህም የአገልግሎታቸውን ቀጣይነት ገሃድ ያደርግልናል፡፡ ስለሆነም በዲያቆናት አገልግሎት ውስጥ ምህረት ማደረግ፣ ልግሥና፣ ግምባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው። ዲያቆናት እነዚህ አገልግሎቶች በተግባር ላይ የሚውሉበትን ተግባራዊ ሁኔታ ያመቻቻሉ። በቤተክርስቲያናችንም ውስጥ ቃሉ የሰጣቸውን አደራ ለማስፈጸም በትጋት ይሠራሉ።

ሰንበት ትምህርት

መጽሐፍ ቅዱስ አውራ ለሆኑ የሕይወት ጉዳዮቻችን መሪ ብርሃን እንዲሆን በሕብረት ከቃሉ እገዛን መሻት ያስፈልጋል። በዚህ የአገልግሎት መስክ የሰንበት ትምህርት ጠቀሜታ እጅግ የጎላ ነው። በተቻለ መጠን ከእሁድ መልእክት ጋር እየተቀናጀ የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችቶ ምእመኑን ያንጻል። በቤተክርስቲያኒቱ ያሉ የቃሉ አገልጋዮች ጸጋቸውን የሚያካፍሉበት እድል ከመፍጠሩ ባሸገር እርስበርስ ለመተናነጽ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተቻለ መጠን መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ተግባራዊና ታሪካዊ ይዘት ኖሯቸው እንዲሰጡ ያደርጋል።

የቤት ኅብረት አገልግሎት (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት)

ቃሉን ተገቢውን የአተረጓጎም ስልት በመከተል በማጥናት፣ ትክክለኛ ፍቺ እየሰጡ ከሕይወት ጋር በማዋሃድ፣ ተልእኮን ይወጣል። የዝርዝር መጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴን (Inductive Bible study) በመተግበር መጽሐፍ ቅዱስ በትንንሽ የቤት ሕብረቶች እንዲጠና ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ምእመናን እንዲተናነጹ እያደረገም ይገኛል። ምእመናን ጸጋቸውን የሚለዩበት እድል እንዲያገኙ የተማሩበትን የሚያካፍሉበት መስመር እያመቻቸ ያሳድጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሚዛናዊ በሆኑ ርእሰ ጉዳዮች እየተጠና ምእመናን የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል። በየወቅቱ የሚጠኑበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እየመረጠ ጥናቱ እንዲሰናዳና እንዲተገበር ከማድረጉ ባሻገር፣ በተቻለ መጠን አንድ ወጥ ሆነው በየጥናት ቡድኑ እንዲያልቁ እያመቻቸ ሥራውን ይሠራል።

ትምህርትና ስልጠና

በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ የሚመራ፣ ወቅታዊ ጥያቄዎችን መላሽ የሆነ አስተምህሮን በሁነኛ ግብ ቀርጸን ክርስቶስ ተኮር ሕይወት እንዲሰርጽ የበኩሉን ይወጣል። ተዛማጅ የሆኑ አውደ ጥናቶችና፣ ሲምፓዚየሞች፣ እንዲሁም ትምህርቶች እንዲዘጋጁ ያደርጋል፤ ለአድማጮችም ሆነ ለተሳታፊዎች የሚቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤ አወዘጋቢ ጉዳዮች ሲነሱ ውዝግቡ ብስለት በተሞላበት መንገድ እንዲያዝ ርዕሰ ጉዳዮቹ በስፋት የሚታዩበት በጥልቀት የሚተነተኑበትና አቋም የሚያዝበት ሁኔታ ላይ እንዲደርስ ጥረት ያደርጋል፣ ጥልቀት ያላቸው ጥናታዊ ጽሁፎች ለወንጌል ያላቸውን ጠቀሜታ ይቃኛል፣ ለምእመናን መታነጽ የሚወሉበትን መንገድ ይቀይሳል።

የጸሎት አገልግሎት

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጸሎት በምእመናን ሕይወትና ልምምድ እንዲሠርጽ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል፣ የወቅቱን የጸሎት ርዕሰ ጉዳዮች በመቅረጽ የጸሎት ሠራዊት በምልጃ እንዲሳተፉ ያነሳሳል። የኅብር ጸሎት ባሕል እንዲዳብር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ማላጆች የሚበራከቱበትን መንገድ እየቀየሰ ምእመናንን በሙሉ ለጸሎት ለማነሳሳት የበኩሉን ይወጣል። ለሕመምተኞች የሚጸለይበትን ቀጣይ የፈውስ አገልግሎት የሚደራጅበትን ሁኔታ ይቀይሳል ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤ዘወትር እሁድ ከአምልኮ በኋላ የጸሎት እርዳታ የሚሹ ምእመናን እንክብካቤ እንዲያገኙ አገልጋዮችን ያነሳሳል። ከመንፈስ ቅዱስ በመነጨ ምሪት፣ በሁሉን ቻይ ጌታ ፊት በመውደቅ ምላሻችንን ተቀብለን እርሱን ለማክበር መትጋትን የአገልግሎቱ መታያ አድርጎ ይንቀሳቀሳል።

የወጣት ጎልማሶች አገልግሎት (Young Adults)

ቃሉን ማእከል ያደረገ፣ ስሜታቸውን ያገናዘበ አገልግሎት የሚሠርጽበትን መንገድ ያመቻቻል፤ ተግባራዊነቱንም ይከታተላል፤ወጣት ጎልማሶች ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለአደራዎች እንዲሆኑ ብቃት የሚያጎለብቱብን መንገድ ይቀይሳል። ወጣቶች በእምነታቸው ሳያመዛዝኑ የተቀበሉት ብቻ ሳይሆን የራሳቸው እንደ ቃሉ የሆነ አቋም እንዲኖራቸው ተገቢውን ትጥቅ ያቀብላል። ከስሜትና ከግልብ መረዳት ጽዱ የሆነ፣ የሰከነ መንፈሳዊ አቋም የእነርሱነታቸው መገለጫ እንዲሆን ተገቢውን ሁኔታ ያመቻቻል፣ ለዚያም ግብ ይሠራል፡፡ ወጣት ጎልማሶች ከቡድናዊ ግፊትና ከጅምላ አቋም ይልቅ የጌታን ፈቃድ ለግላቸው ፈልገው ማወቅ ለሚችሉበት ሁኔታ አቅጣጫን ይቀይሳል፣ ለተግባራዊነቱም ጠንክሮ ይሠራል። ወጣት ጎልማሶች ከቤተሰብ፣ ከእድሜ እኩዮቻቸው፣ ከቤተ ክርስቲያንና ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር በትብብር በመሥራት ተፈላጊው ለውጥ በአካባቢው እንዲመጣ በቅንጅት የሚሠሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል፣ በመደበኛው የቤተ ክርስቲያን ፕሮግራሞች በማኅበረሰቡ ሕይወት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ለትውልድ ክፈተት ድልድይ በማበጀት ወጣቱ ጎልማሶች እንደ ተቀባይ አቀባይ መንፈሳዊ ተልእኮውን እንዲወጣ ወጣቶችን ለተልእኮ ያበረታታል፣ ለተግባራዊነቱም ይሠራል፡፡ በመሆኑም ቃሉን የሚሰጠውን ጽዳት በመቀበል፣ ለክርስቶስ በሁለንተና የተገዛ ሕይወት በመኖር ተልእኮን ከግቡ ያደርሳል።

የልጆች አገልግሎት

የልጆች አገልግሎት እድሜያቸውን ያገናዘበ ተገቢው የእረኝነት እንክብካቤ  እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።እድሜያቸው የደረሰ ልጆች ተገቢውን የደቀ መዝሙር የክትትል ትምህርት እንዲያገኙ ይተጋል፣ ለተግባራዊነቱም ተገቢውን ጥረት ያደርጋል። ልጆች በቤተ ክርስቲያን እንክብካቤ ሥር እያሉ ከሚያጋጥም ችግር ለመታደግ ሽፋን ይሰጣል፣ እንክብካቤው በቦታው ሳያሰልስ መሰጠቱን ያረጋግጣል። እድሚያቸውን ያገናዘበ ካሪኩለም ቀርጾ መንፈሳዊ እንክብካቤ እንዲያገኙ ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል። የልጆችን ስሜት የሚረዱ አገልጋዮችን በቦታው ላይ በመመደብ አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን ይወጣል። በመሆኑም የልጆች አገልግሎት ሕልም «ወንጌል ሳይበረዝ እንዲቀጥል፣ ልጆችን በሁለንተናዊ እይታቸውና ተልእኳቸው እንዲጎለብቱ የማስቻል አገልግሎት ይፈጽማል።

የቤተሰብ አገልግሎት

እግዚአብሔር በምድር ያቋቋመው ወሳኝ ድርጅት ቤተሰብ ነው። የቤተሰብ አገልግሎት ስለ ትዳርና ቤተሰብ አስተዳደር ተገቢውን ግንዛቤ መስጠት ነው። የትዳር መሥራች እግዚአብሔር ለቤተሰብ ያለውን ዕቅድ በማስገንዘብ የቤተሰብ አባላት ለጤናማ ግንኙነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተገቢውን እገዛ ማመቻቸት ቀዳሚ ሚናው ነው። ምሳሌነት ያለው ቤተሳባዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል በማሳየት ለተግባራዊነቱ የአጥቢያይቱን ቤተሰቦች ማንቀሳቀስ የአገግሎቱ ትኩረት ነው። ጤናማ ቤተሰብን የሚያጎለብቱ መርሆች እንዲሠርጹ በመስኩ ያሉ ምሁራን የሚሰጡትን ገንቢ ሃሳብ ከአጥቢያይቱ የቤተሰብ አባላት ጋር ለማስዋወቅ የቤተሰብ መነቀቂያ ማዘጋጀት ወቅታዊ ተግባራዊ እርምጃቸው ነው። በተጨማሪም ወጣቶች የጤናማ ቤተሰብ ፈለግ እንዲከተሉ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበትን ምቹ ሁኔታ በማሰናዳት የጋብቻ ትምህርት ስልጠናዎችን በተከታታይ ማዘጋጀትና ተፈጻሚነቱንም መከታተል የአገልግሎቱ የተግባር እርምጃ ነው። «ሁሉም በደረጃው እንዲሆን ጤና፣ ክርስቶስ ተኮር ሕይወት እናጎልብት የጠንካራ ቤተሰብ መሠረት ነውና፡፡» በሚል እሳቤ ይመራል።

የእንክብካቤ አገልግሎት (ጉብኝትና ማማከር)

በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉት አባላት እርስበርስ እንዲተዋወቁና እንዲደጋፉ በግንኙነት መረብ አስተሳስሮ ተልእኮ ይወጣል። ምእምናን ባሉበት ሥፍራዎች ሁሉ አዳዲስ የቤት ኅብረቶችን እንዲደራጁ ጉብኝቱ እንዲቀላጠፍ ያደርጋል። የሚጎበኙ ምእመናን ቅደም ተከተል ለማስያዝ አስቀድሞ ተጎብኚዎችን ነጥሎ የማውጣቱን ሥራ በትኩረት ይሠራል:: ለሚጎበኙ ግለሰቦች ሁኔታ የሚመቹ ጎብኚዎችን በጥንቃቄ በመምረጥ ጎብኚና ተጎብኚን የማስተሳሰሩን ሥራ እያቀላጠፈ ለጉብኝት አመቺ ስልት እየነደፈ በተግባር ላይ ማዋል ቀዳሚ የተልእኮው አካል ነው። በተጨማሪም ጎብኚዎች በግል መነሳሳት ሳይሆን ከቤተ ክርስቲያን ተመድበው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ እያመቻቸ ምእመናን ወቅቱን ያገናዘበ እገዛ እንዲቀበሉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ተልእኮውን ይወጣል። የማማከሩንም ሥራ ከአገልግሎት ቢሮው ጋር በመቀናጀት ለመፈጸም የበኩሉን ይወጣል። የነርሶችን አገልግሎትም በመጠቀም ምእመናን ጤና ነክ እንክብካቤ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በመሆኑም «በክርስቶስ ፍቅር ተንቀሳቅሰን፣ ለተቸገሩ ደርሰን፣ የተረሳን አስታውሰን የርህርሄ እንክብካቤ እንሰጣለን፡፡» የሚለውን መርህ ለመተግበር ይሠራል።

ሚዲያ አገልግሎት

የቤተክርስቲያኒቱን ውሳጣዊና ውጫዊ ግንኙነት ውጤታማ ለማደረግ የዘመነ የኮምኒኬሽን አገልግሎት እንዲጎለብት በትጋት እየሠራ ይገኛል። በቀደሙት ዘመናት በቴፕ፣ በሲዲ፣ በቪሲዲ፣ በዲቪድ የመነቃቂያ ፕሮግራሞች ላይ የተቀዱትንም ሆነ በመደበኛ ፕሮግራም ላይ የተቀዱትን ፕሮግራሙ ላመለጣቸው ምእመናን ተባዝተው ቀለል ባለ ዋጋ እንዲደርሳቸው በማድረግ አገልግሎቱን ሲያበረክት ቆይቷል። በየወቅቱ ዜና ቤተክርስቲያንንም ሆነ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንተና የሚሰጡ የኅትመት ሥራዎች እንዲሠራጩ የበኩሉ ሲፈጽም ቆይቷል። በውስጡም የኦዲዮቪዥዋል፣ የቪዲዮ፣ የድምፅ፣ የበይነ መረብ፣ የቴፕ፣ የኅትመት፣ የትርጉም አገልግሎቶችን በማደራጀት አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን ያለሰለሰ ጥረት አድርጓል። ሳምንታዊው መደበኛ አገልግሎት በኢንተርኔት በቅርብና በሩቅ ላሉት በቀጥታ ሥርጭት እንዲደርሳቸው እያደረገ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ነው። በመሆኑም ለአያሌ ዓመታት የሚመራበት መርህ «በህብር እንቅስቃሴያችን ፍቅሩን ማስተጋባት ነው ግባችን፡፡ የየፊና ደርሻችንን ተወጥተን መልእክታችንን ለተቀባዮቹ እናደርሳለን፡፡» የሚል ነው።

ወንጌል ሥርጭት

በጥናትና በስልት በተደገፈ መንገድ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወንጌል በመስማት እንዲድኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ መልእክቱ እያደረሰ ወይም እንዲደርስ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህንንም ከባቢያዊና ራቅ ባሉት መካከል ሚዛን በጠበቀ መንገድ ለማድረግ ይተጋል። በተጨማሪም የወንጌል አዋጁ ያስገኛቸውን አዲስ አማንያን እንክብካቤ የሚያገኙበት ሥርዓት ዘርግቶ ተገቢውን የክትትል ትምህርት እያገኙ የሚያድጉበትን መንገድ አመቻችቶ በመሥራት ላይ ነው። በየጊዜውም ለልዩ ልዩ ተልእኮ ፈጥነው የሚደርሱ ግብረ ኃይል ያደራጃል። ወንጌልን ልዩ ልዩ ስልቶችን (ድራማ፣ስነጽሁፍ፣ ፊልም ወዘተ…) በመጠቀም እንዲተላለፍ ሲያደርግ ቆይቷል እያደረገም ይገኛል፡፡ወንጌልን ከማድረስ አኳያ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችና አውደጥናቶች እንዲሰጡ በማድረግ ለወንጌል ሥርጭት መተግበር የበኩሉን ለመወጣት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። አውራ የተልእኮውም ትኩረት «የማዳኑ ወንጌል ያለማቋረጥ በማወጅ፣ ኃጢአተኛውን ለንስሐ እናዘጋጅ» የሚል ነው።

ሚሲዮናዊ ተልእኮ

በወንጌል ያልተደረሱ ሕዝቦችን ለይቶ ለማወቅ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ፣ መልእክተኞች እንዲላኩ የምልጃ ጸሎት እያደረገ መልእክተኞች የሚላኩበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በተጨማሪም በወንጌል ያልተደረሱት ሕዝቦች የሚደረሱበት ስልት እየቀየሰ በትግበራው ጉዳይ ይተጋል። ሚሲዮናዊ ተልእኮ እንዲጎልበትና የሚላኩትን ለማደራጀት ተገቢውን ስልጠና ያቀናጃል ይተገብራል። በየጊዜውም ለአጭርና ለረጅም ጊዜ ሚሲዮናዊ ተልእኮ ተሳታፊዎችን ለሚመለመሉበትና በተግባር ለሚሳተፉበት ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ይንቀሳቀሳል። በተጨማሪም ሚሲዮናዊያንንና ግብአቶችን በተገቢው መንገድ ለማስተሳሰር አስፈላጊውን የማንቀሳቀስ ሥራ ይሠራል። አውራ ትኩረቱም «መልእክቱን ወዳልተደረሱ ሕዝቦች ለማድረስ፣ ሚሲዮናዊ ተልእኮን ማእከል አድርገን እንንቀሳቀስ» የሚል ነው።

መዋዕለ ነዋይ

ከመዋዕለ ነዋይ ጋር የተያያዘው አገልግሎት ቀዳሚ ትኩረት ቤተ ክርስቲያን ማበልጸግ ሳይሆን የገንዘብ አቅሟ የሚገነባበትንና አገልግሎቷ የሚቀላጠፍበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በግብአት እጦት አገልግሎቷ እንዳይገደብ በአቅሙ ያሉትን ሁሉ ለማድረግ ይተጋል፣ በመሆኑም «ሌሎች ጌታን በማፍቀር ያለማቋረጥ እንዲሰጡ፣ ንብረቶቻችን ሁሉ በተገቢው ሁኔታ ይቀመጡ» በሚል ትኩረት ተልእኮውን ይፈጽማል።

አስተዳደር

ቤተ ክርስቲያን ሁልአቀፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴን የምታደርግ ድርጅት ናት፡፡ በመሆኑም እንቅስቃሴዋን ለመተግበር ተገቢው አስተዳደራዊ፣ ፋይናንስ አቅርቦት ከእሁድ የሚሻገር አገልግሎት እንድትሰጥ ይረዷታል፡፡ አስተዳዳር ሥራና ሠራተኛውን በማገናኘት የዕለት ተዕለቱን እንቅስቃሴ ያቀላጥፋል፡፡ ቢሮው ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትሰጠውን ፈርጀ ብዙ አገልግሎቶች እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ፈርጀ ብዙ ከሆኑት የለት ተዕለት ፍላጎቶች ጋር የሚጣመሩ መጠነ ሰፊና አያሌ ገጽታ ያላቸው ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በመሆኑም «ገንዘብን ሎሌ አድርጎ በመግራት፣ ክርስቶስን ያማከለ ሥርዓት መዘርጋትን» ስልቱ አድርጎ ተልእኮውን ይወጣል።

ሁለንተናዊ አገልግሎት

እንደሚታወቀው ሁለንተናዊ አገልግሎት ወንጌሉን ለሰው ሁለንተና ተዛማጅ በሆነ መንገድ ማቅረብ ነው (በ1ተሰ 5፡23 መንፈስን፣ ነፍስንና ሥጋን ማገልገል ነው፡፡ ከሌሎች ፍጥረታት ለየት ባለ መንገድ ሰው በተፈጥሮው የሦስትዮሽ ገጽታ እንዳለው በመረዳት ድርጊት ለበስ አገልግሎት ለመስጠት የበኩልን መወጣት ነው፡፡ መጽሐፉ ከሥጋ የተለየ ነፍስ የሞተ ነው (ያዕ 2፡14) እንዳለው ከሥራ የተለየ እምነትም እንዲሁ እንደሆነ ተገንዝበን የመንግሥቱን አጀንዳ በተግባር ለበስ አገልግሎት ለማስፈጸም እንተጋለን፡፡ በመሆኑም «መንፈስ በሥጋ ውስጥ እንዲኖር አውቀን፣ ለሁለንተናዊ አገልግሎት እንተጋለን፡፡»

የፓራዳይም ወጣቶች አገልግሎት

ቤተክርስቲያናችን የአንድ ትውልድ ቤተክርስቲያን እንዳትሆን ተገቢ ትኪን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን አምና ተግባራዊ እንቅስቃሴን ታደርጋለች። ከአራት አሥርተ ዓመት በላይ ያስቆጠረችው ቤተክርስቲያናችን አንድ የሁለተኛ ትውልድ ቤተክርስቲያን ከውስጧ ወጥቶ ቤተክርስቲያን እንድትተከል ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች። ቀዳማይ ፓራዳይም የወጣቶች አገልግሎትን በማስታጠቅ ሌሎችን በወንጌል እንዲደርሱ የአገልግሎት አድማሳቸው ከአበሻው ማኅበር ባሻገር እንዲሆን በማሰብ የቤተክርስቲያን ተከላን በማመቻቸት ጎጆ አውጥታለች። በዚህ ታሪካዊ ወቅት ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወንጌልን እየሰሙ እንዲታነጹ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አገልግሎት በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተሰጠ በድጋሚ የወጣቶች አገልግሎት እየጎለበተና አካባቢውን እየደረሰ ይገኛል። በዚህ መስመር አገልግሎት በወጣቶች ፓስተር እየተመራ ቤተክርስቲያናዊ አገልግሎቱ ቀጥሏል። ስለዚህ ቀጣይ ትውልዱ ተቀብሎ እንዲያቀብል መስመሩ ተበጅቷል።