የዲቁና አገልግሎት
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዲያቆናት አገልግሎት ብቅ ያለው በጊዜው የተከስተ ችግር ለመፍታት ጥረት በተደረገ ጊዜ ነበር (የሐዋ 6፡1-6)፡፡ ከዚያም በኋላ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን ተልእኮ ለመወጣት የዲያቆናት የአገልግሎት ድርሻ ወሳኝ ሚና እንዳለው ሲታሰብ አግሎግሎቱ በዚያን ወቅት አዲስ በተተከሉ ቤተ ክርስቲያናትም ቀጠለ፡፡ ታሪካቸው ሲጀምር ከሐዋርያት ጋር ተደጋጋፊ ሆኖ ማገልገል ነበር፡፡ በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን ሂደት ዲያቆናት ተጠሪነታቸው ለሐዋርያት ሆኖ መንፈሳዊውን አገልግሎት በማቀላጠፍ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ የሐዋርያት አገልግሎት በሂደት በሽማግሌ፣ በእረኛ ወይም በኤፒስ ቆጶስ በተተካ ጊዜ ዲያቆናት ከሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት አገልግሎታቸውን እንደተወጡ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስተምረናል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምናየቸው ቢሮዎች የሽማግሌዎችና የዲያቆናት ቢሮዎች ናቸው (ፊሊጵ 1፡1) ፡፡ ይህም የአገልግሎታቸውን ቀጣይነት ገሃድ ያደርግልናል፡፡ ስለሆነም በዲያቆናት አገልግሎት ውስጥ ምህረት ማደረግ፣ ልግሥና፣ ግምባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው። ዲያቆናት እነዚህ አገልግሎቶች በተግባር ላይ የሚውሉበትን ተግባራዊ ሁኔታ ያመቻቻሉ። በቤተክርስቲያናችንም ውስጥ ቃሉ የሰጣቸውን አደራ ለማስፈጸም በትጋት ይሠራሉ።